Fana: At a Speed of Life!

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል 100ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከዛሬ ጀምሮ ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ ዓመት እና አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 100ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር) በሰጡት መግለጫ÷ በተቋማት ግንባታ የትውልድ ቅብብሎሽ የሀገርን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡

የሁለቱ ተቋማት እዚህ መድረስ የትውልድ ቅብብሎሹን እንደሚያሳይ ጠቅሰው፤ ዩኒቨርሲቲው ለጤናው ዘርፍ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ባለውለታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከመጀመሪያው ትውልድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ጎንደር የኒቨርሲቲ አንድ ምዕተ ዓመት ካስቆጠሩ የሀገሪቷ ውስን ተቋማት መካከል አንጋፋው መሆኑን አንስተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከምስረታው ጀምሮ ለሀገሪቷ ዘርፈ ብዙ ለውጥ ድርሻው የጎላ እንደነበር፣ ከሕክምና እስከ ግብርና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብዙ እና ጉልህ አበርክቶዎች እንዳሉትም ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምስረታ ከሕዝብ ፍላጎት የመነጨ እንደነበር ጠቅሰው÷ በተለያዩ ጊዜየት ስያሜውን እየቀየረ አገልግሎትና ተልዕኮውን እያሰፋ ዓመታትን ማስቆጠሩንም ተናግረዋል።

እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዘርፍ ያከናወናቸውን ተግባራት ለማስፋት 12 የምርምር ማዕከላት መቋቋማቸውን አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባለፊት ዓመታት ከ100 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እንዳስመረቀም በመግለጽ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ የዩኒቨርሲቲው ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ የካበተ ልምድ እንዳለው ጠቅሰው÷ ከ150 በላይ የውጭ ሀገራት ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ አሁን ለደረሰበት ስኬት ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የምስረታ በዓል አከባበር ከጥር 13 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያልም ብለዋል በመግለጫቸው።

በታሪኩ ለገሰ እና በምናለ አየነው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.