ከ100 ሚሊየን ብር በሚልቅ ወጪ የቅርስ ጥገናና ጥበቃ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በያዝነው የበጀት ዓመት ከ100 ሚሊየን ብር በሚልቅ ወጪ ላይ የ20 ቅርሶች ጥገናና እንክብካቤ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ የተግባር ሥራዎች እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ከእነዚህ ቅርሶች መካከል እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ መኖሪያ ቤት እና ሥዕል ይሠሩበት የነበረ ስቱዲዮ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝዬም እድሳት እንደሚገኙበት ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡
ሌሎቹ ጥገና እየተደረገላቸው የሚገኙት ቅርሶች ደግሞ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እና ድሬዳዋ አሥተዳደር እንደሚገኙ በባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሃፍታሙ አብርሃ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
አሁን የተመደበው 100 ሚሊየን ብር ቅርሶችን በሚፈለገው ልክ ለመጠገን በቂ እንዳልሆነ እና ለከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የማሻገር ሥራ ማከናወንን ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ጥገና ለማከናወን በዕቅድ ተይዘው የነበሩ ቅርሶች የሚገኙባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ችግር መኖሩ እና የገንዘብ እጥረት በአሠራር ላይ ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውንም አመላክተዋል፡፡
ለቅርስ ጥገና እና እንክብካቤ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ ቅርስ መጠገን ለመንግሥት ብቻ የሚተው ኃላፊነት ስላልሆነ÷ ክልሎች፣ ተቋማት እና ሌሎች አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው