Fana: At a Speed of Life!

ከሕዳሴ ግድብ 1 ሺህ 950 ቶን የዓሣ ምርት ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሰው ሠራሽ ሐይቅ 1 ሺህ 950 ቶን የዓሣ ምርት መገኘቱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

በቢሮው የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ ይርጋ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ ባለፉት 6 ወራት የዓሣ ሃብት ልማትን ለማስፋፋት በትኩረት ተሰርቷል።

በተለይም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚከናወነውን የዓሣ ሃብት ልማት ለማጠናከር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።

እስካሁን በግድቡ 74 ማህበራት ተደራጅተው ዕውቅና የተሰጣቸው መሆኑን ጠቅሰው፥ ከእነዚህ መካከል 28 ማህበራት ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ማህበራቱ በዓሣ ማስገሪያ መረብና በዓሣ ምግብ አሰራር እንዲሁም ዓሣ የማስገር ክህሎት እንዲያዳብሩ የሚያስችል ተግባር ተኮረ ስልጠና መሰጠቱን አንስተዋል።

ለዓሣ ማስገሪያ የሚውሉ 29 ጀልባዎችና 1 ሺህ 400 መረቦችን ማቅረብ መቻሉን ጠቁመው፥ በግማሽ ዓመቱ ከሕዳሴ ግድብ 1 ሺህ 947 ቶን የዓሣ ምርት ማምረት መቻሉን አስረድተዋል።

የዓሣ ምርቱ 12 ፍሪጅ በተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች አማካኝነት ለአዲስ አበባ ገበያ እየቀረበ መሆኑንም አብራርተዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.