ኢትዮጵያና አርጀንቲና የአየር አገልግሎት ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና አርጀንቲና በአየር አገልግሎት ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ እና የአርጀንቲና አየር ትራንስፖርት ዘርፍ ዋና ጸሃፊ ፍራንኮ ሞጌታ ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመንገደኛና የጭነት በረራ አገልግሎት ከኢትዮጵያና አርጀንቲና መዳረሻ ጣቢያዎች በተጨማሪ በአርጀንቲና ግዛት ውስጥ እንዲሁም ወደ የትኛውም 3ኛ ሀገር መዳረሻ ጣቢያ መብረር ይችላል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ሁሉንም የትራፊክ መብቶችና ገበያው በፈቀደ ልክ ያለምንም ገደብ በማንኛውም አውሮፕላን አይነት የበረራ ምልልስ የማድረግ መብትን እንደሚያጎናጽፍ ተጠቁሟል፡፡
መደበኛ ያልሆኑና የቻርተር በረራዎችን ያለገደብ መብረር የሚያስችል መብት የሚሰጥ መሆኑንም የባለስልጣኑ መረጃ ያመላክታል፡፡