የአገው ፈረሰኞችን በዓል በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ለሚከበረው የአገው ፈረሰኞች ማህበር ምስረታ በዓል አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል፡፡
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ለይኩን ሲሳይ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የአገው ፈረሰኞች በዓል በጣልያን ወረራ ወቅት ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር የተዋደቁ ጀግኖች አርበኞችንና ፈረሶቻቸውን ለመዘከር ታልሞ የሚዘጋጅ ነው፡፡
የዘንድሮውን የአገው ፈረሰኞች ማህበር ምስረታ በዓል በእንጅባራ ከተማ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
የማህበሩ አባላት በዓሉን በድምቀት ለማክበር ለፈረሶቻቸው አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ልምምድ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡
ነባር የማህበሩ ፈረሰኞች ስልጠና በመስጠት ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው÷ ይህም ወጣቶች ተሞክሮ እንዲወሰዱ ማስቻሉን አንስተዋል፡፡
የእንጅባራ ከተማ አገልግሎ ሰጪ ተቋማት በበዓሉ ለሚታደሙ እንግዶች አስፈላጊውን መስተንግዶ ለመስጠት ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የአገው ፈረሰኞች ማህበር ክብረ በዓልን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ማህበሩ ከ65 ሺህ በላይ አባላት ያሉት መሆኑን አቶ ለይኩን አስገንዝበዋል፡፡
በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችም በበዓሉ እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ