ፓርቲው እኩል የፖለቲካ ተሳትፎና የህዝብ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ ነው – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልፅግና ፓርቲ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በኢትዮጵያ እኩል የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
ፓርቲው የፖለቲካ ስብራትን በመጠገን የህዝቦችን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያከናውናቸው ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዋናና አጋር በሚል ቀድሞ የነበረውን አደረጃጀት በማስቀረት ብሔር ብሔረሰቦች ውክልና ኖሯቸው እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን አስገንዝበዋል።
ፓርቲው የልዩነት ግንቦችን በመናድ በሀሳብ ትግል ብቻ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እውን እንዲሆን በማድረግ የሴራ ፖለቲካን ወደ መርህ ፖለቲካ በመቀየር የመገፋፋት እና ጥላቻ ፖለቲካን ወደ ሰላምና አብሮነት የቀየረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህም ብልፅግና በአካታችነቱ እና ሰው ተኮር የልማት ስራዎቹ ቅቡልነት በማግኘታቸው በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች በሀገሪቱ ብሎም በሐረሪ ክልል ታላላቅ ስኬቶችን ማስመዝብ የቻለ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
በክልሉ በኢኮኖሚው መስክ በቱሪዝም እና በግብርና ልማት ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።
በማህበራዊ ልማት ረገድ በትምህርትና ጤና ዘርፎች የተለያዩ ስራዎች ማከናወን መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ አክለዋል።
በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ አበረታች ስኬቶችን በውጤት አጅቦ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ መግለፃቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡