Fana: At a Speed of Life!

ብልጽግና ፓርቲ የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራት እያከናወነ ነው-ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት እያከናወነ ነው ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ፡፡

ከለውጡ በፊት የነበረው ጊዜ እርስ በርስ መገፋፋት፣ መጠላለፍ፣ አግላይ ፖለቲካ የሚታይበትና እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ያልተከተለ ነበር ብለዋል።

በተለይ እንደ ጋምቤላ ክልል አጋር ድርጅት በሚል ስያሜ በሀገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የመወሰን መብት የተነፈገበት እንደነበርም አስታውሰዋል።

ሁሉን ያቀፈው የብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተ ወዲህ በሀገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋት በመምጣቱ ቀደም ሲል የነበረው አግላይነት በማስቀረት ጋምቤላን ጨምሮ ሌሎች ክልሎች የልማቱ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል።

ጋምቤላ ክልል ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ ሠላምና መረጋጋት ያለበት ክልል የነበረ ቢሆንም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ግን የፀጥታ ችግር በጣም ፈታኝ የሆነበትና የክልሉን የልማት መሻት በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይጓዝ አድርጎት መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም ነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም. በክልሉ አዲስ የአመራር ለውጥ በማድረግ በክልሉ ተፈጥሮ የነበረውን ጫፍ የወጣ የብሔር ፅንፈኝነት የፈጠረው የጥል ግርግዳ ለማፍረስና ዕርቀ-ሰላም ለማውረድ ከከተማው ጀምሮ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኘው አመራር የተሳተፈበት ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል ነው ያሉት፡፡

በልማቱ ረገድም ክልሉ በርካታ ሊለማ የሚችል ለም መሬት እንዳለው ገልጸው÷ ከዛሬ 4 ዓመት በፊት ይታረስ የነበረ የእርሻ መሬት 112 ሺህ 826 ነጥብ 95 ሔክታር እንደነበር አውስተዋል፡፡

ከዚህም 2 ሚሊየን 39 ሺህ 87 ነጥብ 20 ኩንታል ምርት ይገኝ እንደነበር መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

በ2016 የምርት ዘመን ከ125 ሺህ 706 በላይ ሄክታር መሬት በማረስ ከ3 ሚሊየን 188 ሺህ 503 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት እንደተቻለም አስረድተዋል፡፡

በመጠጥ ውሃ አቅርቦት የጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በ8 ከተሞች ብቻ የነበው፤ አሁን ላይ አንዳንድ የመንገድ መሠረተ-ልማት ካልደረሰባቸው የአኮቦ ወረዳ እና አንዳንድ አካባቢዎች በስተቀር በክልሉ 13 ከተሞች የመጠጥ ውኃ አቅርቦት መኖሩን ጠቁመዋል።

በገጠር ከከተማ የተሻለ የውሃ ተደራሽነት መኖሩን እንዲሁም በጋምቤላ ከተማ ያለውን የቆየ የውሃ ችግር ለመቅረፍ ሲባል በነባሩ ፕሮጄክት ላይ የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ በከተማው 01 እና 02 ቀበሌዎች እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው÷ በቀጣይ ችግሩን ቀርፎ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከለውጡ በፊት የጎሬ-ጋምቤላ-ላሬ-ፓጋግ የአስፋልት መንገድ ብቻ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተጀመሩ 612 ነጥብ 24 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው 8 የመንገድ ፕሮጄክቶች መኖራቸውንም አብራርተዋል።

ጋምቤላ- አቦቦ-ፒኝውዶ እና ፒኝውዶ-ጊሎ ወንዝ በተሻለ ደረጃ ላይ ሲገኙ፤ የአፈፃፀም ደረጃቸው በጣም ዝቅተኛ የሆኑትን እንደ አኩላ-አቻኛ-ዲማ/ራድ፣ ላሬ-ጂካዎ-ኝንኛንግ እና ጎግ-ጆር-አኮቦ ያለባቸው ችግር ተቀርፎ በቀጣይ ግንባታቸው እንደሚፋጠን አመላክተዋል፡፡

ሌሎች የተቋረጡ ጋምቤላ-ኢሊያ፣ ኢሊያ-መኩዌይ፣ አቦቦ-ሜጢ-ኩቢጦ ማዞሪያ ለረዥም ጊዜያት የቆሙ መሆናቸውን በመግለጽ በቀጣይ እንደሚጀመሩና የህዝቡ ጥያቄ እንደሚመለስ ጠቁመዋል፡፡

በወርቅ ማዕድን ልማት በ2011 በጀት ዓመት ከነበረበት 122 ነጥብ 24 ኪሎ ግራም ዓመታዊ የወርቅ ምርት በ2016 በጀት ዓመት 225 ኪሎ ግራም ወርቅ ምርት መገኘቱን አስታውሰዋል።

በክልሉ አዲስ የአመራር ለውጥ ከተደረገ በኋላ በተሰጠው ልዩ ትኩረት በ2017 በጀት ዓመት 650 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ታቅዶ በመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ብቻ በተደረገው የአመራር የቅርብ ክትትል 2 ሺህ 747 ኪሎ ግራም ከ520 ግራም ከዓመቱ ዕቅድ በላይ ለብሄራዊ ባንክ ገቢ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በ2011 በጀት ዓመት 603 ሚሊየን 811 ሺህ 694 ነጥብ 88 የነበረውን የገቢ መጠን በ2016 በጀት ወደ 1 ቢሊየን 626 ሚሊየን 785 ሺህ 523 በማሳደግ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡

በቀጣይ በመፍጠንና በመፍጠር ጥበብ የተረጂነት አስተሳሰብን ለማስቀረት የተጀመሩ ኢኒሼቲቮችን ውጤታማ ለማድረግ ሙሉ የአመራር ቁመና ላይ መሆን፤ አገልጋይ የአመራርነት ስነምግባር መላበስና ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማምጣት አመራሩ የሚገጥሙትን ችግሮች ወደ ዕድል በመቀየር ያመለጡንን ወርቃማ ዕድሎች ለማካካስ በጊዜ የለንም ስሜት በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉም አስታውቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.