ብልጽግና ፓርቲ ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ከምንም በላይ ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የፓርቲው አመራሮች ገለጹ።
ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት፣ ሀገራዊ የልማትና የብልጽግና እቅዶች ለማሳካትም የተጀመሩ ሁለንተናዊ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አለማየሁ ባውዲ፤ ፓርቲያችን ከምንም በላይ ሰላምን ያስቀድማል ለልማት ደግሞ ሌት ተቀን ይተጋል ብለዋል።
በዚህም ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፖለቲካ ምህዳርን በማስፋትና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርቲው በአንደኛ ጉባዔው ያስቀመጣቸው የጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት፣ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል የመገንባት ትልሙ ጥሩ ውጤት የታየበት መሆኑንም ተናግረዋል።
በፓርቲው የድሬዳዋ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኢብራሂም የሱፍ፤ ከምንም በላይ ለሰላምና ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም ተጨባጭ ውጤቶች መምጣታቸውን ገልጸው፤ የሀገርን ሁለንተናዊ ልማትና ብልጽግናን ለማሳካት ጥረትና ርብርቡ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ለሀገር ልማት፣ ለፍትሃዊና የጋራ ተጠቃሚነት እውን መሆን ብልጽግና ፓርቲ ሰፊ ጥረት ማድረጉን አስታውሰው፤ በቀጣይም ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ ይደረጋል ሲሉ አረጋግጠዋል።
በፓርቲው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው፤ ከለውጡ በኋላ በሁሉም መስኮች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
በተለያየ ጊዜ ተጀምረው የነበሩ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት በማብቃት ረገድ የታየው አፈፃፀም የሚደነቅ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡