ክልሉ 21 ሺህ 877 ቶን ቅመማቅመም ለማዕከላዊ ገበያ አቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 21 ሺህ 877 ቶን ቅመማቅመም ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረቡን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አስታወቀ፡፡
የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር እና የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማትና ጥበቃ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ኮጁአብ÷ ክልሉ ለቅመማቅመም ልማት ቢያመችም የህግ ማዕቀፍ እና ወጥነት ያለው የግብይት ስርዓት አለመኖር ያለውን አቅም አሟጦ ለመጠቀም እንዳላስቻለ ገልጸዋል።
ይህ እንዳለ ሆኖ ክልላዊ የቅመማቅመም ሽፋን 140 ሺህ ሄክታር መድረሱን ጠቁመው፤ በበጀት አመቱም ተጨማሪ 38 ሺህ 732 ሄክታር መሬት በቅመማ ቅመም ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት 13 ሺህ 535 ሄክታር መሬት በቅመማቅመም መሸፈን መቻሉን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በስድስት ወሩ 18 ሺህ 434 ቶን ቅመማቅመም ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 21 ሺህ 877 ቶን በማቅረብ ከዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን አመልክተዋል፡፡
በቀሪው የበጀት ዓመቱ ጊዜ የታቀደውንም ሆነ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ቅመማቅመም በስፋት የሚመረት ሲሆን፤ ኮረሪማ፣ ጥምዝ፣ ቁንዶበርበሬ፣ ዝንጅብል፣ ሂልና እርድ በብዛት ከሚመረቱት መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
በፌቨን ቢሻው