Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት አስቸኳይ ጉባዔውን አካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት 3ኛ ዓመት 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ወደ ሃላፊነት የመጣው መጅሊሱ በርካታ ስኬታማ ተግባራትን አከናውኗል።

እነዚህን ሥራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል ከጥቂት ወራት በኋላ ለቀጣይ 5 ዓመታት ተቋሙን የሚመሩ የአዳዲስ አመራሮች ምርጫ በመላ ሀገሪቱ ይካሄዳል ብለዋል።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ በዛሬው ጉባዔው የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን÷በዚህም የተዘጋጀ የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያና ማስፈጸሚያ ሰነድን አጽድቋል፡፡

እድሜው ለምርጫ የደረሰ ሁሉም ሕዝበ ሙስሊም በአካባቢው በሚገኝ መስጂድ በመመዝገብ በምርጫው በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል።

ሕዝበ ሙስሊሙ ምርጫውን ሽፋን በማድረግ አንድነቱን አደጋ ላይ ከሚጥሉ እንቅስቃሴዎች እራሱን እንዲጠብቅ መልዕክት የተላለፈ ሲሆን÷ ምርጫውን ለማከናወን የሚያስችል በጀት መጽደቁም ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በጉባዔው የፌዴራል የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ አባላት ምርጫ የተካሄደ ሲሆን÷አባላቱ ቃለ መሃላ መፈጸማቸው ተጠቅሷል፡፡

በመድረኩ የክልልና ከተማ አስተዳደር እስልምና ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚና የምክር ቤቱ አባላት እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.