ባንኩ አሰራሩን ሊያሻሽል እንደሚገባ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አሰራሩን ሊያሻሽል እንደሚገባ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመላከተ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የብድር አሰጣጥና አጠቃቀም ስርዓት ላይ ከፌደራል ኦዲተሮች፣ ከልማት ባንክ አስረጂዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
ውይይቱ የተካሄደውም የፌዴራል ኦዲተር ጄኔራል በ2015/16 በጀት ዓመት ባካሄደው የኦዲት ግኝቶች መነሻ ላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሽመቤት ደምሴ (ዶ/ር) ÷በ2014 የዘርፉ ፖሊሲ ቢሻሻልም፣ የልማት ባንኩ የፖሊሲ ማስፈጸሚያ መመሪያ የሌለው መሆኑን በመግለጽ ፖሊሲውን መሰረት ያደረገ መመሪያ እስከ የካቲት 30 ፀድቆ ወደ ስራ መግባት እንዳለበት አሳስበዋል።
በተጨማሪም ባንኩ የተበዳሪዎችን ማንነት ከገቢዎችና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ማረጋገጥ እንደሚገባው አስረድተዋል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ሃይሌ በበኩላቸው÷የልማት ባንክ የማምረቻ ብድር አሰጣጥና አመላለስን በተመለከተ ኦዲት ሲያደርጉ ሶስት የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጠው እና 44 መስፈርቶችን በመለየት ኦዲቱን ከ2013 እስከ 2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ድረስ ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።
ባንኩ በርካታ ሪፎርሞችን ማካሄዱን ጠቅሰው÷በቀጣይ የበለጠ ውጤታማ ሆኖ እንዲሄድ ከተፈለገ የባንኩ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የተቀመጡ ሕጎችን አክብረው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አንስተዋል።
ባንኩ ክፍተቶችን ለመሙላት ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ዋቄ ናቸው፡፡
በመድረኩ በናሙና የተጠቀሱ ብድሮች ወይም ፕሮጀክቶች ላይ ክፍተቶች እንደነበሩ ቀደም ብለው ያወቁ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ክፍተቱንም ለማስተካከል ባንኩ ስትራቴጂ አውጥቶ ሲሰራ እንደነበር መግለጻቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
የደንበኞችን መረጃ በጥልቀት በመመርመርና አሰራሩን በዲጂታል በመደገፍ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።