የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር የስፖርት ስብራትን ለመጠገን ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር የስፖርት ስብራትን ለመጠገን ጉልህ ድርሻ እንዳለው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
”የታዳጊ ስፖርተኞች ልማት ለአሸናፊ ሀገር” በሚል መሪ ሐሳብ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው፡፡
በሲምፖዚየሙ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሐመድ÷የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር የስፖርት ስብራትን ለመጠገን ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ከመገንባትና ከማመቻቸት አንፃር ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሲምፖዚየሙ ስፖርት ለሀገራዊ ብልጽግና ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ፣ ለመልካም ገፅታ ግንባታ፣ ለዲፕሎማሲ እና ለስፖርት ዘርፍ ቱሪዝም የሚጫወተውን ሚና ማጉላት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ነውም ተብሏል፡፡
ላለፉት 5 ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር መጀመሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት መንገድ እንደሚከፍትና ለስፖርት ዘርፉ ለውጥ ለማምጣት ዕድል እንደሚፈጥርም ተመላክቷል።
በመድረኩ በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ገለፃ መደረጉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኩሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በመርሐ ግብሩም የክልል ቢሮ ኃላፊዎች፣የብሔራዊ ስፖርት ማህበራት ፕሬዚዳንቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡