የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎቹን ለኮሚሽኑ አስረከበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሊካተቱ ይገባሉ ያላቸውን አጀንዳዎች በዛሬው ዕለት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በይፋ አስረክቧል፡፡
በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ ኮሚሽኑን ወክለው ንግግር ያደረጉት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ÷ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱ ለኮሚሽኑ ዓላማ መሳካት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ ማኅበረሰቡ ስለ ኮሚሽኑ ተግባራት መረጃ እንዲያገኝ በማድረግ እንዲሁም የሚዲያ ተቋማትን ሀገራዊ አጀንዳዎች አደራጅቶ በማስረከቡ ምክር ቤቱን አመስግነዋል፡፡
በቀጣይ የምክክር ሂደትም ምክር ቤቱ ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው÷ምክር ቤቱ በሥነምግባር የታነጸ ሚዲያ በኢትዮጵያ እንዲጎለብት የሚሠራ ተቋም ነው ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ በስድስት ርዕሰ ጉዳዮች የተከፋፈሉ የኢትዮጵያ እንዲሁም የሚዲያ ኢንዱስትሪውን መሠረታዊ ችግሮች የሚፈቱ አጀንዳዎች መዘጋጀታቸውን አአመላክተዋል፡፡
ምክር ቤቱ ከሀገራዊ ምክክሩ ጋር የሚተሳሰሩ ጉዳዮችን ወደ ሕዝብ ለማስረጽ በትኩረት መሥራቱን እንደሚቀጥልም ማረጋገጣቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡