በሃላይደጌ-አሰቦት ዕጩ ብሔራዊ ፖርክ የተከሰተውን እሳት ለመቆጣጠር ርብርብ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሃላይደጌ-አሰቦት ዕጩ ብሔራዊ ፖርክ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለማስቆም ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽ/ቤቱ ሃላፊ አቶ አሕመድ ኢድሪስ እንደገለጹት÷ ሦስተኛ ቀኑን የያዘውን ሰደድ እሳት ለማጥፋት የአሚበራ ወረዳ መስተዳድርና የአካባቢው ማህበረሰብ ርብርብ ቢያደርጉም እስካሁን ድረስ እሳቱን መቆጣጠር አልተቻለም።
እሳቱን የማጥፋት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ሃላፊው÷ እሳቱ በሰው ሃይል ብቻ ስለማይጠፋ ወደሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ በሎደር የታገዘ እሳት የማጥፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በአካባቢው ያለው ከፍተኛ ንፋስና ደረቅ ሣር መብዛት ለእሳቱ መባባስ ምክንያት መሆኑን ጠቁመው÷ ተቀጣጣይ ነገሮችን ከአካባቢው የማፅዳትና የማራቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
እሳቱ በፖርኩ ማዕከል “ጎልባ” በተሰኘና የዱር እንስሳት መኖሪያ አካባቢ መከሰቱን ነው የጠቆሙት፡፡
የፓርኩ አጠቃላይ ስፋት 1ሺህ 99 ስኩዌር ኪሎ ሜትር እንደሆነ የገለጹት ሃላፊው÷ እስካሁን ድረስ ከ200 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የነበረ ሣርና ቋጥ በእሳቱ ጉዳት ይደርስበታል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል።
የእሳት አደጋው መንስኤና የደረሰው ጉዳት መጠን በቀጣይ ተለይቶ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸው÷ እሳቱን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ እየተደረገ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡