Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ዣዎ ማኑኤል ጎንሳልቬስ ሎሬንስ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንጎላ ፕሬዚዳንት ዣዎ ማኑኤል ጎንሳልቬስ ሎሬንስ የ2025 የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።

“የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ እና ነገ የሚካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።

ካለፈው ዓመት የህብረቱ ሊቀመንበር የሞሪታኒያ ፕሬዚዳንት መሀመድ ኦሊድ ጊዞኒ ሃላፊነቱን የተረከቡት ፕሬዚዳንት ዣዎ ማኑኤል ጎንሳልቬስ ሎሬንስ፤ ሀገራቸው አንጎላ በሊቀመንበርነቷ ለአህጉራዊ ዕድገት ትኩረት ትሰጣለች ብለዋል።

በተለይም በግብርና፣ ብሉ አኮኖሚ ሰላም እና ጸጥታ እንዲሁም ሌሎች መስኮች ላይ እንደሚሰሩ ገልጸው፤ አፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ የሰፈነባት እንድትሆን ግጭቶች እንዲቆሙ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የፈጠረውን እድል በመጠቅም በአህጉሩ የተሳለጠ የንግድ ትስስር እንዲኖር ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም አመላክተዋል።

ሀገራቸው በአህጉሪቱ ለሚከናውኑ ዋና ዋና ፕሮግራሞች እና ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል ፋይናንስ ለማሰባሰብ ከህብረቱ ጋር በጋራ እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

በተባበሩት መንግስታት የሚከናወኑ ተቋማዊ ማሻሻያዎች ለአፍሪካ ጥቅም ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

በመሳፍንት ብርሌ እና ሔለን ታደሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.