የኢትዮጵያን የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችውን ሒደት በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የዓለም ንግድ ድርጀት አባል ለመሆን ጥረት እያደረገች መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
የድርጅቱ አባል ለመሆን የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ለማጠቃለል እየተሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገቻቸው በሚገኙ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ዙሪያም ለዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ባስጠበቀ መልኩ የድርጀቱ አባል እንደምትሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመላክተዋል፡፡