ከ5 ሺህ በላይ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ተመረቁ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 5 ሺህ 828 ዜጎችን የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ የሚያደርጉ የካራ ዱስና ካራ ቆርጮ የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፕሮጀክት ፖርትፎሊዮ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክንፈ ነጋሽ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ፕሮጀክቶቹ 425 ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም አላቸው፡፡
የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቹ ለአካባቢው ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው አንስተዋል፡
የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ዘላቂነት እንዲኖራቸውም ማህበረሰቡ በተገቢው መልኩ ሊገለገልባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኤሌክትሪክ አገልግሎትን በገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ ማድረግ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተገልጿል፡፡
በቀጣይ የኤሌክትሪክ አገልገሎትን በገጠር ቀበሌዎች የማስፋፋቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መጠቆሙንም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡