Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ የፌዴራል ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ማሰባሰብ የሚሳተፉበትን መድረክ ለማዘጋጀት እየተሰናዳ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በፌዴራል ደረጃ በምክክር ሂደቶች እንዲሳተፉ ከለያቸው ባለድርሻ አካላት አጀንዳ ለማሰባሰብ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በሂደቱም ኮሚሽኑ በፌዴራል (በሀገር አቀፍ) ደረጃ ከሚገኙ ተቋማትና ማህበራት አጀንዳ የሚሰበስብ ሲሆን መርሃ-ግብሩም በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ ይከናወናል፡፡

ኮሚሽኑ ላለፉት ወራት በ10 ክልሎች እና 2 የከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ ሲያሰባስብ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ በሚካሄደው መድረክ በድምሩ 17 ከሚጠጉ የፌዴራል ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ አጀንዳዎችን ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡

በሂደቱም የሚከተሉት ባለድርሻ አካላት ጥሪ እየተደረገላቸው ሲሆን ተቋማቱ በወኪሎቻቸው አማካኝነት በሂደቱ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት፣ የሰራተኞች ማሕበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የአረጋውያን ማሕበራት ፌዴሬሽን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲ) መምህራን፣ የመምህራን ማሕበር፣ የአሰሪዎች ፌዴሬሽን፣ የአካል ጉዳተኞች ማሕበራት ፌዴሬሽን፣ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ታዋቂ ሰዎች ይሳተፋሉ።

እንዲሁም የፌዴራል መንግስት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የፌዴራል ፍርድ ቤት፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ተሳታፊ እንደሚሆኑ የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.