የዓድዋ ድል የአፍሪካውያን የድል አድራጊነት ምሳሌ ነው – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓድዋ ድል የአፍሪካውያን የድል አድራጊነት ምሳሌ ነው ሲሉ በም/ ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
አቶ አደም ፋራህ ለ129ኛውን የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የጀግንነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት ፋና ወጊ፤ የአፍሪካውያን የድል አድራጊነት ምሳሌ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል እና የሰው ልጅ የፅናት ምልክት መሆኑን ያወሱት አቶ አደም÷ ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል ያስተማረንን የጋራ እሴቶች፣ መከባበርና መተባበር ላይ በመመስረት፣ ጠንካራ፣ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁላችንም በዓርበኝነት ስሜት በቁርጠኝነት እንትጋ ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡