የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለዓድዋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ለ129ኛውን የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በመልዕክታቸው÷የዓድዋ ድል በኅብረብሔራዊ አንድነት የተገኘ ታላቅ የተጋድሎ ድልና የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ቀንዲል መሆኑን አንስተዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)÷ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን አንድነትና ትብብር ያተየበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ድሉ ለሁሉም አፍሪካውያን ኩራት፣ በጽናት ሀገርን ማሻገር የሚቻልበትን ትክክለኛ መንገድ ያስተማረ ነው በለዋል፡፡
የዓድዋን ድል ዛሬም በድህነትና ኋላቀርነት ላይ ዳግም በመዝመት የኢኮኖሚ ስብራትን መጠገን በምንችልበት አቅም ሁሉ ርብርብ ልናደርግ ይገባናል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ ድል የወረሰውን የጀግንነት ታሪክ ድህነትን በማሸነፍ ሊደግም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያን የጋራ አጀንዳ ማድረግ የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ከኋላ ቀር የነጠላ ትርክት በመውጣት በገዢ ትርክትና ህብረ ብሔራዊነት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ነው ያስረዱት፡፡
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኦሞድ÷የዓድዋ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር ቀኝ ገዢዎች በጥቁር ሕዝብ ተሸንፈው ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካ የነፃነት አዲስ ምዕራፍ የከፈቱበት ታሪካዊ በዓል መሆኑን አስታውሰዋል።
የዓድዋ ድል ሁሉንም ኢትዮጵያውያን አንድ ከማድረግ ባለፈ ከራስ ፍላጎት ይልቅ የሀገር ፍቅር ቀድሞ የታየበት ትልቅ የአብሮነት እሴት እንደሆነም አንስተዋል።
የዓድዋ ድል መላው ጥቁር ሕዝብ ለነጻነቱ እንዲነቃቃ ማድረጉን ገልጸው÷ በየዓመቱ ለድል በዓሉ እየተሰጠ ያለው ትኩረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡