ኢትዮጵያና አርጀንቲና በአቪዬሽን ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ በኢትዮጵያ ከአርጀንቲና አምባሳደር ኢግናሲዮ ሮካታግሊያታ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ከአንድ ወር በፊት በአርጀንቲና ቦነስአይረስ በአጭር ፊርማ ደረጃ የተጠናቀቀውን የአየር አገልግሎት ስምምነት በሙሉ ፊርማ ደረጃ የሚጠናቀቅበት ሂደት እንዲፋጠን ከመግባባት ደርሰዋል፡፡
በተጨማሪም በአርጀንቲና በአውሮፕላን ማምረት፣ ጥገናና ምህንድስና የተሰማራው FAdeA የተሰኘ ኩባንያ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ለመክፈትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ከባለስልጣኑ ጋር በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና አርጀንቲና በአለም አቀፋ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመንቀሳቀስ ትኩረት ሰጥተው ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው የተነሱትን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የውይይት መድረክ እንዲመቻች መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡