በዳውሮ ዞን የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ ለኢንቨስትመንት በር ከፋች መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዳውሮ ዞን ባለፈው ጥር ወር ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ለአካባቢው የኢንቨስትመን ፍሰት በር ከፋች መሆኑ ተገልጿል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቀው የኢቲ-ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ለበርካታ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩንም የዳውሮ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ አስታውቋል።
የመምሪያው ኃላፊ ኃይሌ ዱባለ የድንጋይ ከሰል ግብዓት የሚያቀርቡ 14 ድርጅቶች ለማህበረሰቡ የሚጠበቅባቸውን የንግድና ኢንቨስትመንት ክፍያ በመፈጸም ፈቃድ ወስደው በማምረት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ በፍቃዱ አሰፋ በበኩላቸው፤ ፋብሪካው ለሲሚንቶ ፋብሪካ ግብዓት በማቅረብ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በተኪ ምርት ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት የራሱን አዎንታዊ ሚና እየተጫዎተ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢቲ-ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ በዓመት ከ450 ሺህ እስከ 500 ሺህ ቶን ከፍተኛ ጥራት ያለውን የታጠበ የድንጋይ ከሰል ለሲሚንቶ ፋብሪካ በማቅረብ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን 25 በመቶ የመሸፈን አቅም እንዳለውም ተገልጿል።