Fana: At a Speed of Life!

አዲስ የኢንዱስትሪ ማሕበረሰብ እየተፈጠረ ነው- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ አዲስ የኢንዱስትሪ ማሕበረሰብ መፈጠሩን አመላካች ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ሆሚቾ የጥይት ማምረቻ ፋብሪካን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ባደረጉት ንግግር፤ አዲስ የኢንዱስትሪ ማሕበረሰብ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

ከመከላከያ ሠራዊት ዋና ዋና የሪፎርም አቅጣጫዎች መካከል በመከላከያ ትጥቅ ራስን መቻል አንዱ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁን ላይ ዐቅም መገንባቱን አረጋግጠዋል፡፡

የሆሚቾ የጥይት ማምረቻ ፋብሪካን ዘመኑ በደረሰበት የዲጂታል ሥርዓት ውስጥ በማስገባት፤ ለከባድ፣ ቀላልና መካከለኛ መሣሪያዎች የሚያገለግሉ ተተኳሾችን ማምረት ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡

በኢንዱስትሪው የተፈጠረው ዐቅም ከሀገሪቱ የአቅርቦት ፍላጎት በላይ መሆኑን ያነሱት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ የውጭ ገበያንና ትውልድን ታሳቢ ተደርጎ መገንባቱን አስረድተዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.