ኢትዮጵያ እና ስዊድን በትብብር በሚሠሩበት ጉዳይ ላይ ምክክር ተደረገ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሥራ እና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በኢትዮጵያ ከስዊድን አምባሳደር ሃንስ ሄንሪክ እና የስዊድን የስደተኞች ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ዋና ፀሐፊ አንደርስ ሆል ጋር ተወያዩ፡፡
በዚሁ ወቅትም በክኅሎት ልማትና ሥራ ዕድል ፈጠራ የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ወደ ስዊድን ስለሚሰማራበት ሁኔታ መክረዋል፡፡
በኢንተርፕሪነርሺፕ ሥነ-ምኅዳር ግንባታ ዘርፍ በቅንጅት መሥራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ በዝርዝር መወያየታቸውንም ሚኒስትሯ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
በተመረጡ የትብብር ማዕቀፎች ላይም በጋራ ለመሥራት ከስምምነት መድረሳቸውን ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ እና ስዊድን በትምህርትና ሥልጠና መስክ የረዥም ጊዜ ትብብር እንዳላቸው ገልጸው፤ አሁን የተጀመረው ሥራም ይህንን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
አምባሳደሩ እና ዋና ፀሐፊው በክኅሎት ልማትና ሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ በትብብር ለመሥራት ላሳዩት ቁርጠኝነት ሚኒስትሯ አመሥግነዋል፡፡