የኮሙኒኬሽን ዘርፉ በብሔራዊ ትርክት ግንባታ የላቀ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮሙኒኬሽን ዘርፉ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማረም፣ አፍራሽ አጀንዳዎችን በመመከትና በብሔራዊ ትርክት ግንባታ የላቀ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ “ዓላማ ተኮር፤ የተናበበ እና የተቀናጀ የተግባቦት ሥርዓት ለእመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሐሳብ በመካሄድ እየተካሄደ ነው፡፡
ሚኒስትሩ በመድረኩ ላይ በዓላማ ተኮር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አስፈላጊነት ላይ ባደረጉት ገለፃ፥ የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ነባራዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ በአግባቡ መመራት እንዳለበት አንስተዋል።
የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ያለውን ፖለቲካዊ እና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ዐውድ ተረድቶ በመምራት ለውጤት መብቃት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሀገርን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የዲፕሎማሲ አካሄድና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ በቅንጅት መሥራት እንደሚጋባም አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የኮሙኒኬሽን ዘርፉ የቀውስ ጊዜ የመረጃ አሥተዳደር ስልት ተቀርፆ መተግበር እንዳለበት ጠቁመው፤ የተሳሳቱ መረጃዎችን ማረም፣ አፍራሽ አጀንዳዎችን መመከትና ከሁሉም ቀድሞ መገኘት ይገባል ብለዋል።
በብሔራዊነት ትርክት ግንባታ፣ የመንግሥት የፖሊሲ ትግበራ በትክክለኛ መንገድ እንዲተገበር በማድረግ እና ሀገራዊ መግባባት በሚፈጥሩ አጀንዳዎች ዙሪያ ተከታታይ ሥራዎችን መሥራት ከዘርፉ ይጠበቃል ነው ያሉት።
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እና መረጃ በሁሉም አማራጭ ተደራሽ መደረጉን ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል።