የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር ET-302 አደጋ ተጎጂዎች የመታሰቢያ ሃውልት ተመረቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር ET-302 አደጋ ተጎጂዎች 6ኛ ዓመት የመታሰቢያ ሃውልት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET-302 መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ኬንያ ለመብረር በተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በመከስከሱ የተሳፋሪዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡
በዛሬው ዕለትም የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜን (ዶ/ር) ጨምሮ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ አምባሳደሮች፣ የተለያዩ እንግዶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ለተጎጂዎች የመታሰቢያ ሃውልት ተመርቋል፡፡
አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷የደረሰው የአውሮፕላን አደጋ መቼም ሊረሳ የማይችልና በልባችን ውስጥ ያለ ትልቀ ሃዘን ቢሆንም የአየር ትራንስፖርትን ደህንነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንድንሰራ ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል።
የደረሰው አደጋ እጅግ አሳዛኝ እና አስከፊ በመሆኑ ሃዘኑን መግለጽ ከባድ እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡
ከዚህ አስከፊ አደጋ በኋላ የአለም አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ደህንነትን ለማጎልበት፣ የአውሮፕላን ዲዛይን ለማሻሻል እና ቁጥጥር ለማጠናከር ጉልህ ርምጃዎችን እንደወሰደ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው÷ለአደጋው ተጎጂዎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀው፤ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።
አደጋው ቅድሚያ ለደህንነት ሰጥተን መስራት እንዳለብን ትምህርት ያገኝንበት ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
አደጋ ከተከሰተ ጀምሮ መታሰቢያ ሃውልቱ እስከሚሰራ ድረስ የአከባቢው ማህበረሰብ ላደረገው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።