Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ እና አውሮፓ ሕብረት ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ

‎አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ሕብረት መካከል ያለውን ትብብር እና ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ።

በኔዘርላንድስ የኢትዮጵያ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን የፕሮቶኮል ዋና ዳይሬክተር ፔርኒላ ሾውሊን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ሕብረት መካከል ያለውን ትብብር እና ስትራቴጂያዊ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተመላክቷል።

ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የጋራ ጥቅሞችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ ለመሥራት የሚያስችሉ መንገዶች ዙሪያም ምክክር ተደርጓል።

አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በውይይቱ ወቅት÷ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኝነት እንዳላት ገልጸዋል።

በአውሮፓ ሕብረት ተቋማት ውስጥ የጋራ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ እንደሚሰሩም መናገራቸውን ከብራስልስ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ዋና ዳይሬክተሯ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ቁርጠኝነት በማሳየት ረገድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ያለውን ጠቀሜታ አብራርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.