በ5 ቢሊየን ብር ለሚገነባው የብሉ ፋይበር ቦርድ ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡኢ ከተማ በ5 ቢሊየን ብር ለሚገነባው የብሉ ፋይበር ቦርድ ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
17 ሺህ 304 ሄክታር መሬት በሚሸፍን ቦታ ላይ የሚገነባው ፋብሪካው በዓመት 150 ሺህ ሜትር ኪዩብ የእንጨት ውጤቶች ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል።
ፋብሪካው ስራ ሲጀምር ለ1 ሺህ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተመላክቷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የመሰረት ድንጋይ ከማኖር ስነ-ስርዓቱ በኋላ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በከተማዋ የተገነቡ የችፑድ ፋብሪካዎችን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።