2 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ አማራ ክልል መጓጓዙ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ለ2017/18 የምርት ዘመን መኸር ወቅት የእርሻ ሥራዎች የሚውል እስካሁን 2 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መጓጓዙን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡
በቀጣይ የመኸር ወቅት በክልሉ 186 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
በምርት ዘመኑ እስካሁን 5 ነጥብ 4 ሚልየን ሄክታር የሚጠጋ መሬት መታረሱን ተናግረዋል።
ከግብዓት አቅርቦት አንጻር 8 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ገልጸው፤ እስካሁን 2 ሚሊየን ኩንታል የሚሆነው ወደ ክልሉ ተጓጉዟል ብለዋል።
በክልሉ ከደረሰው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው ለተጠቃሚው መሰራጨቱንም ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በክልሉ ሁሉም ዞኖች የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ንቅናቄ እስከ መጋቢት 30 እንደሚከናወን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በበጋ መስኖ ስራዎች በበጋ ስንዴ ለመሸፈን ከታቀደው 230 ሺህ ሄክታር ውስጥ 200 ሺህ ያህሉ መሸፈኑን ገልጸው፤ በቀጣዮቹ ጊዜያትም ግቡን ማሳካት የሚያስችሉ ስራዎች በትኩረት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።