Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል የከተሞች የኮሪደር ልማት የዜጎችን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል እየተከናወነ የሚገኘው የከተሞች የኮሪደር ልማት ፍትሃዊ ልማት ለዜጎች እንዲደርስ እድል መፍጠሩን የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ በቀለ እንደገለጹት÷ በክልሉ በሚገኙ 732 ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

የኮሪደር ልማት ስራው በከተሞች መሰረተ ልማትን በተቀናጀ መልኩ ማስፋፋት፣ የከተሞችን ፕላን በዘመናዊና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማዘጋጀት ያለመ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የከተማን ውበትና ጽዳት በመጠበቅ የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በከተማዎቹ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከመጀመራቸው በፊት ከህብረተሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት መካሄዱን ጠቁመው÷ በዚህም በኮሪደር ልማት ስራው ብዙ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማቱ በተለይም በከተሞች የእግረኛ መንገድ፣ አመቺ በሆኑ ቦታዎች የብስክሌት መንገድ የመገንባት ስራ፣ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች፣ የጎርፍ ማስወገጃ ቦይ፣ የአረንጓዴ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የውሃ፣ መብራትና ቴሌ መሰረተ ልማቶችን በተቀናጀ መልኩ መገንባትን ባከተተ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮሪደር ልማት ስራው ያሉትን የትራንስፖርት አማራጮች ለማስፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ የከተማን ውበት ለማጎልበት በርካታ አጋዥ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በኮሪደር ልማት ስራው ከሁሉም በላይ ከተሞች ቱሪዝምና ኢንቨስትመንትን መሳብ የሚችሉ እንዲሆኑ እያገዘ እንደሆነ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ እየተከናወነ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሃዊ ልማት ለዜጎቸ እንዲደርስ እድል እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.