የኢትዮጵያን አየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት ከመጠበቅ ባለፈ ታሪክን የማደስ ተግባራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን- ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን አየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት ከመጠበቅ ባለፈ ታሪክን የማደስ ተግባራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አስታወቁ።
ዋና አዛዡ ከ37 ዓመት በላይ ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ የቆየውንና የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማሪያም ይንቀሳቀሱበት የነበረውን DHC-5 Buffalo አውሮፕላንን ጥገና በማድረግ ወደ ሥራ ያስገቡ ኢንጂነሮችና ቴክኒሺያኖችን አመስግነዋል፡፡
ሌተናል ጄኔራል ይልማ በዚህ ወቅት÷ አውሮፕላኑ ሙሉ ጥገና የተካሄደለት እና ከዘመኑ ጋር የተዋሃዱ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጥገና የተደረገለት አውሮፕላኑ በተደጋጋሚ ሙከራ ወደ አየር ሃይል እንዲቀላቀል በመደረጉ መደሰታቸውን ገልጸው÷ይህም በተቋሙ የሚመራመሩና ቴክኖሎጂን የሚያሳድጉ ወጣቶች መኖራቸውን ያየንበትም ነው ብለዋል።
መከላከያ ትጥቆችን ከመግዛት በተጨማሪ አምራች ለመሆን እያደረገ ባለው ጥረት አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቁመው ÷አንጋፋው አየር ሃይልም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
ለታላቅ ሀገር፤ታላቅ የአየር ሃይል በሚል መሪ ሃሳብ የተገነባው አየር ሃይሉ የኢትዮጵያን የአየር ክልል ከመጠበቅ ባለፈ ታሪኩን በማደስ ሀገራዊ አቅም የመሆን ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡
የካናዳ ስሪት የሆነው የDHC-5 Buffalo አውሮፕላን የኢትዮጵያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ከሀገር ሲሸሹ እስከ ኬንያ የሄዱበት አውሮፕላን መሆኑ ታሪካዊ ያደርገዋል ማለታቸውንም የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመላክታል።