በጾሙ ወራት የነበሩ መልካም ተግባራትን ማጠናከርና የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍ ይገባል- ምክር ቤቱ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በመልዕክቱም፤ በጾሙ ወራት የነበሩ መልካም ተግባራትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ሠላም በሚያፀኑና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ተግባራትን በማከናወን የትንሳኤ በዓልን ማክበር እንደሚገባ ገልጿል፡፡
የምክር ቤቱ መልዕክት ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡-
የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በዓል አደረሣችሁ ሲል የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፏል!
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መዳን ሲል መከራን ተቀብሎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎና ቤዛ ሆኖ እውነተኛ ፍቅሩን ለሰው ልጆች ገልጿል፤ ሞትን ድል አድርጎ በመነሳት የሰውን ልጅ ከዘላለማዊ ኃጢያት ነፃ አውጥቷል፡፡ እሱ በከፈለው መስዋዕትነት ለሰው ልጅ ሁሉ መዳን ሆኗል።
ስለሆነም የክርስትና እምነት ተከታዮች ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መዳን ሲል የከፈለውን መከራ፣ ስቃይና ሕማማቱን እያሰቡ በየዓመቱ ትንሣኤውን ያከብሩታል።
በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ የስቅለትና የትንሳኤ በዓል ልዩ ሥፍራ ይይዛል።
ረጅሙን የዐቢይ ፆም ወራት በፆም በፀሎት አሳልፈው፤ አርብ ላይ ሆነው እሁድ ትንሳኤውን እያሰቡ ሰሙነ ሕማማቱን እጅግ ውብ በሆኑ ሐይማኖታዊ ሥርዓቶችን አሳልፈው በዓለ ፋሲካን ያከብራሉ፡፡
በተመሣሳይ በሌሎች ቤተ እምነቶችም እንዲሁ የዐቢይ ፆም ጊዜን በፆምና በፀሎት የሚሳልፉ ሲሆን፤ የትንሣዔ በዓሉንም በልዩ ልዩ መልኩ ያከብሩታል።
የትንሣኤ በዓል ወይም የፋሲካ በዓል የፀብ ግድግዳ ፈርሶ በፈጣሪና በሰው ልጆች መሀል እርቅ የሆነበት፣ የሰው ልጆች ምህረት ያገኙበት፣ እውነተኛ ሠላምና ደስታ የተገለፀበት ነው፡፡
ስለሆነም የፋሲካ በዓልን ስናከብር በይቅርታ፣ በምህረትና በዕርቅ ውስጥ ሆነን ሊሆን ይገባል።
በፆሙ ወራት ያሳየነውን መልካም ተግባራትን በማጠናከር ያጡና የተቸገሩ ወገኖችን በማሳብና ፍቅር በመስጠት፣ የኢትዮጵያን ሠላም በሚያፀኑና አብሮነታችንን የሚያጠናክሩ ተግባራትን በማከናወን ልናከበር ይገባል፡፡
በዓሉ የሠላም የፍቅርና እውነተኛ ደስታ የሚገለፅበት እንዲሆን ምክር ቤቱ ይመኛል!
የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤