Fana: At a Speed of Life!

ርዕሳነ መሥተዳድሮች የትንሳዔ በዓልን አብሮነትን በማጽናት ማሳለፍ እንደሚገባ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ ክልሎች ነገ ለሚከበረው የትንሳዔ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከትንሳዔው ፈተናን በጽናት መሻገር፤ ጨለማን ወደ ብርሃን መቀየር እንደሚቻል እንረዳለን ብለዋል፡፡

ዛሬ ያጋጠሙን ችግሮችም ለትውልድ የማይሻገሩ፣ የሚታለፉና የሚፈቱ ናቸው ያሉት አቶ አረጋ፤ ፈተናዎችን ወደ እድል ለመቀየር የሕዝባችንን ሰላም ማጽናትና ልማታችንን ማፋጠን አለብን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ባህላችን እና ሐይማኖታዊ እሴታችን በሚፈቅደው መሠረት፤ የተቸገሩ ወገኖቻችን በማሰብ በአብሮነት እና በመተባበር ማሳለፍ አለብን፤ በዓሉም የሰላም፣ የጤና፣ የደስታና የፍቅር ይሁንልን ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በመልዕክታቸው፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳትና በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነትንና ኅብረ-ብሔራዊነትን የሚጠይቅ በመሆኑ፤ በዓሉን ስናከብር በፍጹም ኢትዮጵያዊ ባህል መሆን አለበት ብለዋል፡፡

በክልሉ ለተጀመረው የሰላም ግንባታና የለውጥ ጉዞ ስኬታማነት ምዕመኑ የበኩሉን እንዲያበረክትም ጥሪ አቅርበዋል።

ለተቸገሩ ወገኖች ዐቅም የፈቀደውን በማካፈልና እርስበርስ በመተሳሰብ በዓሉን ማክበር እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ናቸው፡፡

በዓሉ ዘመድ አዝማድ ተሰባስቦ በፍቅርና በአብሮነት የሚያከበርው መሆኑን አውስተው፤ ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን የሰላምና የደስታ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.