ኢትዮጵያ ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኗ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በግብርና ልማት ሥራ እያስመዘገበች ያለው ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆን የግብርና ሚኒስትር አማካሪ ዜና ኃብተወልድ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የግብርና ልማት ፕሮግራም የተሻለ አፈፃፀም እንዳላት እና ፕሮግራሙ ያስቀመጣቸው መስፈርቶችን በልማት ዕቅዷ በማካተት ተግባራዊ ማድረጓ ለውጤቱ መገኘት ትልቅ ድርሻ አበርክቷል ብለዋል፡፡
በስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በሌማት ትሩፋትና በሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎች እያስመዘገበች ያለው ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ማታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በኢጋድ የምግብ ሥርዓት ፕሮግራም አስተባባሪ ሠናይት ረጋሳ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የኢጋድ አባል ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ሥራ ለመከወን እያደረጉ ያለውን ጥረት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ድጋፍ እየተደረገ ነው።
ፕሮግራሙ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የግብርና ፖሊሲዎች አሠሪ እንዲሆኑ እና የተደራጀ የመረጃ ሥርዓት አያያዝ ላይ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡
ግብርናን ማዘመንና በቴክኖሎጂ የማገዙ ሥራ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።