በ10 ከተሞች የዲስትሪቢዩሽን መስመር መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት ሥራ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዲስትሪቢዩሽን መስመሮች እርጅና ምክንያት በከተሞች እያጋጠመ ያለውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመቅረፍ በተመረጡ 10 ከተሞች የዲስትሪቢዩሽን መስመር መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ሥራ ለመስራት ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረገው፤ በነቀምት፣ አምቦ፣ ሱሉልታ፣ ቢሾፍቱ፣ አሰላ፣ ደብረ ብርሃን፣ ዲላ፣ ሆሳዕና፣ አሶሳ እና በጅግጅጋ ከተሞች መሆኑን አገልግሎቱ ለፋና ዲጂታል አስታውቋል፡፡
በሦስት ምዕራፍ ተከፍሎ የሚከናወነው ፕሮጀክቱ፤ በመጀመሪያው ዙር ቢሾፍቱ፣ ሱሉልታ እና ደብረ ብርሃን፤ በሁለተኛው ዙር አሰላ፣ ሆሳዕና፣ ዲላ እና ጂግጅጋ እንዲሁም በሦስተኛው ዙር አምቦ፣ ነቀምት እና ኦሶሳ ከተሞችን ይሸፍናል ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ 200 አዳዲስ ትራንስፎርመሮችን የመትከል፣ 1 ሺህ ትራንስፎርመሮችን የማሻሻል እና 1 ሺህ 103 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ቮልቴጅ መስመር የማስፋፊያና የማሻሻያ ሥራን እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡
የፕሮጀክቱ የገንዘብ ምንጭ የዓለም ባንክ ሲሆን፤ ሥራውን ለማጠናቀቅም 54 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መመደቡ ተመላክቷል፡፡
የፕሮጀክት ግንባታ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ዓለም አቀፍ ተቋራጮችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ዙር ለሚገነቡት የደብረ ብርሃን፣ ሱሉልታ እና ቢሾፍቱ ከተሞች የፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት ኤ ዊልኪንስ ከተሰኘ ኢንጅነሪንግ ኩባንያ ጋር ውል በመፈፀም ወደ ሥራ መገባቱ ተጠቁሟል፡፡
በቀጣይ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቅቀው ወደ አገልግሎት ሲገቡ በ10 ከተሞች ውስጥ በ100 ኪሎ ሜትር መካከለኛ መስመሮች ላይ የሚኖረው አማካይ የመቆራረጥ ድግግሞሽ ቅነሳ 45 በመቶ እንዲሁም በ100 ኪሎ ሜትር አማካይ የኃይል መቆራረጥ ቆይታ 50 በመቶ እንዲሆን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዮሐንስ ደርበው