የትምህርት ማስረጃን የማጣራት አገልግሎት የሚያቀርቡ መተግበሪያዎች ወደ ስራ መግባታቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ማስረጃን የማጣራት አገልግሎት የሚያቀርቡ መተግበሪያዎች ወደ ስራ መግባታቸውን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ገለጸ።
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ላበለጸጋቸው አዳዲስ ሶፍትዌሮች እውቅና የመስጠትና በቀጣይ ስራዎችን በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፥ ተቋሙ አሰራሩን ዲጅታላይዝ በማድረግ ለደንበኞቹ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ ነው።
ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ አዳዲስ መተግበሪያዎችን በማበልጸግ ወደ ስራ ማግባቱን እና በቅንጅት የበለጸጉት አዳዲስ መተግበሪያዎች አገልግሎቱን ለማዘመን ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የመተግበሪያዎቹ የትምህርት ማስረጃን የማጣራት፣ ወደ ሌላ ተቋም የመላክና ሌሎች አገልግሎቶችን በፍጥነት ለደንበኞች ለማቅረብ የሚያስችሉ እንደሆኑም ጠቁመዋል።
በቀጣይም ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር የፈተና አስተዳደርና የምዝገባ ስርዓቱን ማዘመን የሚያስችሉ መተግበሪያዎችን ለማበልጸግ ይሰራሉ ብለዋል።
አገልግሎቱ ከ34 ሚሊየን በላይ ዜጎችን መረጃ መያዙን በማንሳት እነዚህን መረጃዎች በተፈለጉበት ፍጥነት ለደንበኞች ለማድረስ መተግበሪያዎቹ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑም አስረድተዋል።
የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ መተግበሪያው የአገልገሎቱን አሰራር በማዘመን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታና የተደራጀ መረጃን ለመያዝ የሚያስችል እንድነሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።