Fana: At a Speed of Life!

የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሥርጭትን ለመቆጣጠር ርብርብ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጋምቤላ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የጋራ ርብርብ እንዲደረግ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ከ ሲ ዲ ሲ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ፍኖተ ካርታን ለባለድርሻ አካላት አስተዋውቋል።

ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ በዚሁ ወቅት፤ መንግሥት የሕብረተሰቡን ጤና አገልግሎት አስተማማኝ ለማድረግና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት በማከናወን ለውጥ ማምጣት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የኤች አይ ቪ ኤድስን ሥርጭት ለመግታት ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በመለየትና የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን በማዘጋጀት የተሠራው የመከላከል ሥራ ውጤታማ ነበር ብለዋል፡፡

ይሁን እንጅ በተለያዩ ምክንያቶች የሥርጭት መጠኑ በክልሉ ሊገታ አልቻለም ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

በመሆኑም በቫይረሱ ሥርጭት ምክንያት ዜጎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ሌሎች አዳዲስ ዕቅዶችን አዘጋጅቶ መከላከል ላይ ያተኮረ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው ያስገነዘቡት፡፡

በዚሁ መሠረት በክልሉ ተግባራዊ የሚደረገው የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ፍኖተ ካርታ አንዱ መፍትሔ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው የሕዝቡን የጤና ሁኔታ ያረጋግጣል ተብሎ የታመነበት በመሆኑ፤ አመራሩ የተቀመጡትን የመፍትሔ አቅጣጫዎች በአግባቡ ተግባራዊ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.