በኮሪደር ልማትና መልሶ ማልማት ስራ የልማት ተነሺዎች አስደናቂ ትብብር አድርገዋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኮሪደር ልማትና መልሶ ማልማት ስራ የልማት ተነሺዎች አስደናቂ ትብብር አድርገዋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል።
በስብሰባው ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባቀረቡት ሪፖርት የኮሪደር ልማት እና መልሶ ማልማትን ጨምሮ በርካታማ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን በመሰረታዊነት እያደሰ መሆኑን ገልጸው፤ በኮሪደር ልማት መኪና መንገድ ብቻ ሳይሆን 80 በመቶ በላይ ተሽከርካሪ የሌለውን የከተማችን ነዋሪዎች በቀላሉ ሊጠቀሙበት የሚችሉትን የእግረኛ መንገዶችን አስፋፍተናል ብለዋል።
የብስክሌት መንገዶችን ማስፋፋት በመጀመሩም የብስክሌት ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደጋ መምጣቱን አመልክተዋል።
በኮሪደር ልማትና መልሶ ማልማት ስራ የህዝቡ ድጋፍና ትብብር የተረጋገጠበት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ስራ ውስጥ ወጣቶች እና ሴቶች በጉልበታቸው አግዘዋል፤ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን አፍስሰዋል ያሉት ከንቲባዋ፤ የልማት ተነሺዎች አስደናቂ ትብብር አድርገዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገፅታ መቀየሩ እና ምቹ መኖሪያ እንድትሆን ከማድረጉ ጎንለጎን የስራ ዕድል የፈጠረ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በክብረወሰን ኑሩ