Fana: At a Speed of Life!

ወጣቱ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሚናውን እንዲወጣ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው።

የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ እና የኦሮሚያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በመተባበር በ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ወጣቶች የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያስችል የስልጠና መድረክ አዘጋጅተዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በባቱ ከተማ በሚሰጠው በዚህ ስልጠና ከክልሉ ሁሉም ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ወጣቶች ተሳትፈዋል።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ከድር እንዳልካቸው በመድረኩ እንዳሉት፤ ወጣቶች በክልሉ ልማት፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት የድርሻቸውን በማበርከት ላይ ይገኛሉ።

ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ለብሔራዊ ጥቅም መረጋገጥ የወጣቶች አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ከግምት ውስጥ ያስገባ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ እንዲሆን የወጣቶች ድርሻ የጎላ እንደሆነና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ወጣቶች ስለምርጫ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ እንደሚገባቸውም አቶ ከድር ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ ወጣቶች በሰጡት አስተያየት በ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ስኬት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

በአቢይ ጌታሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.