Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ሦስት ዓመታት ለሰብዓዊ ድጋፍ በሚል የገባ ስንዴ የለም – አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ድጋፍ በሚል የገባ የርዳታ ስንዴ አለመኖሩን ከአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።

የኮሚሽኑ ሥራ የአንድ መንግሥት ተቋም ብቻ ሳይሆን ሁሉም ተቋማት ተካተው የድርሻቸውን የሚወጡበት አሠራር የመፍጠር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ ለአደጋ ተጋላጭ እንዳይሆን መጠንቀቅ፣ የተከሰተው አደጋ ጉዳት እንዳያደርስ የማምለጥና የመመከት እንዲሁም አማራጭ መፍትሔዎችን መውሰድ የአደጋ ስጋት አይበገሬነት ግንባታውን ለማሳካት አስተዋጽዖ እንዳለው ገልጸዋል።

ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ለመሸፈን ቀድመን መያዝ ያለበትን ክምችት በመያዝ ለሚከሰተው ማንኛውም ችግር ቀድሞ ለመድረስ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

የአደጋ ስጋት ጉዳዮች ድንበርና ወሰን እንደሌላቸው የገለጹት ኮሚሽነሩ÷ ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲሁም ተቋማት እርስ በርሳቸው ተቀናጅተው የሚሰሩበትን ሥርዓት የሚጠይቅ እንደሆነ አንስተዋል።

ተረጂነት ጠባቂነትና ጥገኝነትና ጎጂ የሆኑና ክብርን የሚነኩ ነፃነትን የሚነኩና ሉዓላዊነትን የሚሸረሽሩ መሆናቸውን ለማስገንዘብና ለማግባባት ሰፊ ስራዎችን በመስራት ወደ 20 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎችን ጨምሮ የመንግስት መዋቅሮችን ያሳተፈ ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል።

ውይይቱን ተከትሎ የማጥራትና የመለየት ሥራዎች በመሰራታቸው የሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊ ቁጥር መቀነሱንም ወደ ፊትም እየቀነሰ ሊሄድ እንደሚችል አመላክተዋል።

በፌዴራል ደረጃ ኮሚሽኑ የቅድሚያ ቅድሚያ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን እንደሚያግዝ አንስተው÷ ሌሎችን ክልሎች እንደሚሸፍኑ ጠቁመዋል።

በዚህም ወደ ዘጠኝ ክልሎች አሁን ላይ ኮሚሽኑ ምንም አይነት መደበኛ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደማይልክና የድጋፍ ፈላጊ ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱ በራሳቸው አቅም እየሸፈኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ተፈናቃይ ላለባቸው ክልሎች እገዛ እንደሚያደርግ በተለይም ትግራይ፣ አማራ፣ አፋርና ሶማሌ ክልሎች አጋር አካላትንም በማሳተፍ መደበኛ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ለሰብዓዊ ድጋፍ ተብሎ ከውጭ የገባ ስንዴ የለም ያሉት አምባሳደር ሽፈራው÷ በራስ አቅም ያለውን ሀብት በማንቀሳቀስና ኅብረተሰቡን በማሳተፍ የሰብዓዊ ድጋፎች እየተሸፈኑ መሆናቸውን አንስተዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.