የስኬት ቁልፍ ትጋት ነው – አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንም የሚያልመው ስኬት ላይ ለመድረስ ተስፋ ባለመቁረጥ ሂደት ቁልፉ ያልተቋረጠ ትጋት መሆኑን ተገንዝቦ መጣር እንዳለበት አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ ትመክራለች፡፡
በሙያዋ አንቱታን እና ተወዳጅነትን ያተረፈችው አርቲስት ዓለምፀሐይ አሁን ለደረሰችበት ክብር ከመድረሷ በፊት በብዙ አድካሚ ውጣውረዶች ማለፏን ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራት ቆይታ አንስታለች፡፡
ይቺ ዘርፈ-ብዙ የኪነ-ጥበብ ሴት፤ በአንድ በኩል ሙሉቀን መለሰ፣ ንዋይ ደበበ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ እንዲሁም ቴዎድሮስ ታደሠን ጨምሮ ለሌሎች በርካታ ስመጥር ዘፋኞች ግጥም ደርሳለች፡፡
ደግሞም የትወና ፈርጥ ናት፤ በተጨማሪም በርካታ ቴአትሮችን በመጻፍ እና በማዘጋጀት የተዋጣላት ናት፡፡ በዚህም ለዓመታት ያለመታከት አገልግላለች፤ አሁንም በፍቅር በምትወደው በዚሁ ሙያ ላይ ትገኛለች፡፡
እንዲሁም ለሀገር በቀል ባህል ዕውቀቶች ያላት ክብር ላቅ ያለነው፤ ለዚህም ጣይቱ የባህል እና ትምህርት ማዕከልን ዕውን ማድረጓ በአስረጂነት ይጠቀሳል፡፡
በዚህም ከሀገረ አሜሪካ እስከ ኢትዮጵያ ጣይቱ የባህል እና ትምህርት ማዕከልን አቋቁማ ብዙ ታትራለች፡፡ ከሰሞኑም በአዲስ አበባ የሚገኘው የትውልድ ሃብት የሆነውን ታሪካዊውን ጣይቱ የባህል እና የትምህርት ማዕከል አድሳ አጠናቅቃለች፡፡
በዚሁ ወቅት ማዕከሉ ቅርስ እንደመሆኑ መጠን ክብሩን በሚመጥን ሁኔታ ይዘቱ ተጠብቆ እድሳቱ እና ተያያዥ ግንባታዎች መከናወናቸውን አስረድታለች፡፡
የዛሬው ጣይቱ የባህል እና ትምህርት ማዕከል፤ ላለፉት በርካታ ዓመታት ለተለያዩ መንግሥታዊ እና ግለሰባዊ አገልግሎቶች ሲውል መቆየቱንም አርቲስት ዓለምፀሐይ አንስታለች፡፡
አሁን ከዕድሳት እና ማስዋብ በኋላ ጣይቱ የባህል እና ትምህርት ማዕከል የሆነው ቤት በ1897 ዓ.ም የተሠራ ሲሆን፤ በወቅቱም የቢትወደድ ኃይለጊዮርጊስ ወልደሚካኤል መኖሪያ ቤት ነበር፡፡
በኋላም ለአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤትነት እና በፍርድ ቤትነት ማገልገሉን ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
በ2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ይሁንታ እና በባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ስምምነት ለአርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ በታሪክ አደራ ጠባቂነት የተሰጠ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም ቤቱ ለጣይቱ የባህል እና ትምህርት ማዕከልነት እንዲያገለግል ውሳኔ ተላልፏል፡፡
ከውሳኔው በኋላም በኢትዮጵያ ሕዝብ፣ መንግሥት፣ ተቋማት እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ድጋፍ የቅርስ ጥበቃን ሕግጋት በመጠበቅ ታድሶ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተመርቆ ተከፍቷል፡፡
በዓመታት ዕድሜው ጉዳት ያስተናገደው ይህ ቅርስ፤ በከፍተኛ ጥንቃቄ ይዘቱ ሳይቀየር የነበሩ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የአሁን ገጽታውን እንዲያገኝ ለማድረግ በዕድሳት፣ በሐሳብ፣ በጉልበት በዲዛይን ከፍተኛ ዋጋ ተከፍሎበታል ብላለች፡፡
ቀደም ባሉ ጊዜያት የዛሬውን ማዕከል ለመቀበል ጥረት ያደረጉ እና ያልተሳካላቸው አካላት እንደነበሩ ጠቁማ፤ እኔ ዕምነት ተጥሎብኝ ስለተሰጠኝ አመሠግናለሁ፤ ከዚህ አንጻር ቅርሱን ከመፍረስ መታደግ በመቻሌም ከፍተኛ ደስታ እና ክብር ይሰማኛል ስትል ገልጻለች፡፡
በተለያዩ ሙያዎች የሚገኙ ግለሰቦች እንዲሁም በክልሎች እና ከተሞች በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት እና የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ትብብር ማድረጋቸውን ጠቅሳ፤ ለዚህም ምሥጋና አቅርባለች፡፡
በሥራዋ ውስጥ ከጊዜያቸው እና ከገንዘባቸው ድጋፍ የማያደርጉ በርካታ ተቺዎች ብሎም ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚጥሩ እንደነበሩ ጠቅሳ፤ ይህን ማለፍ ከሥራው በላይ አድካሚ ነበር ትላለች፡፡
ጥበብ ማሕበረሰብን ለማነጽ ብሎም ለማዝናናት ከፍተኛ ፋይዳ አለው፤ ጣይቱ የባህል እና ትምህርት ማዕከልም ለዚህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክትና ለትውልድ የሚሻገር የጥበብ ቤት መሆኑን በአጽንኦት ታነሳለች፡፡
አሜሪካ በነበራት ቆይታም፤ ኢትዮጵያውያንን የማስከበር እና በሀገሪቱ ለሚኖሩም የኢትዮጵያን ባህል እና ቋንቋ እንዲያውቁ በዚህም እንዲኮሩ በርካታ ሥራዎች መሥራቷን ጠቅሳለች፡፡
ለአብነትም የተለያዩ ሀገርኛ የጥበብ ሥራዎችን ከማቅረብ ባሻገር፤ በአማርኛ ቋንቋ የተለያዩ አገልግሎቶችን በተደራጀ አግባብ ማግኘት እንዲቻል መደረጉን ነው የምትገልጸው፡፡
በሌላ በኩል ካላት ንባብ እና ዓለም አቀፍ ልምዶች በመነሳት ከሕጻናት አምባ በፊት የሕጻናት ቴአትር ቤት እንዲከፈት ጥያቄ ማቅረቧን አውስታ፤ በወቅቱ ምላሹ ሳቅና ስላቅ ነበር ትላለች፡፡
ይሁን እንጅ በኋላ ላይ በቀረበ ተደጋጋሚ ጥያቄ በጉዳዩ ላይ ዕውቀቱ እና የውጭ ሀገራት ልምድ ያላቸው ሰዎችም ታክለውበት መሳካቱን አንስታለች፡፡
በዚህም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ጠንካራ ልጆችን ማፍራት እንደተቻለ ተናግራለች፡፡
ከልጅነት ጀምሮ በቤተሰብ ውስጥ፣ በጎረቤት እንዲሁም በትምህርት ቤት እያየሁት ያደኩት ትጋት እና ፍቅር የአሁኑን ማንነቴን ገንብቷል፤ ያለፍኩበት የዓላማ ጽናትም ከዚያ የሚቀዳ ነው ትላለች፡፡
እቴጌ ጣይቱ ብጡል ለሀገር አንድነት የነበራቸው አቋም፣ ግጭትን ተጸያፊነታቸው፣ ብልኅነታቸው፣ ለዘመናዊ አሥተዳደር ያላቸው ቅርበት፣ ሥልጣኔን ወደ ሀገር ለማምጣት የነበራቸው ንቃት እና ከሀገር ፍቅራቸው አንጻር የነበራቸው ጥርጣሬ ሁሉ እንደሚያስደንቃትም ገልጻለች፡፡
በውጫሌ ውል ስምምነት ወቅትም በአግባቡ እንዲፈጸም የእቴጌይቱ ሚና የጎላ እንደነበር ለአብነት በመጥቀስ፡፡
ለሀገር በቀል ዕውቀቶች ያላቸው ክብር እና ከዘመናዊ ዕውቀቶች ጋር አጣጥሞ ለመቀጠል የነበራቸው ቁርጠኝነት እንደሚገርማትም ነው የምትናገረው፡፡
በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ትልቁ ትርፍ ከሁሉም በፊት ሰው ላይ መሥራት መሆኑንም አስረድታለች፡፡
በጥበብ ሥራ ውስጥ ጊዜን ጨምሮ ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ አንዱ ሌላውን መረዳት እንደሚጠበቅም ታስገነዝባለች፡፡ እንዲህ ካልሆነ ጥበብ የግል ጊዜን ስለሚሻ በትዳር፣ በቤተሰብ፣ በጉርብትና ብሎም በማኅበራዊ ግንኙነቶች ላይ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል አመላክታለች፡፡
ለምሳሌ በኪነ-ጥበብ ውስጥ ላለ ሰው ብቻውን መሆን ሲፈልግ ካልደገፉት በትዳርም ይሁን በቤተሰብ ውስጥ በርካታ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ፍቺ እና ሌሎች መነጠሎችን ጨምሮ ነው የምትለው፡፡
ሕይዎት ያለ ዓላማ ኦና ነው ያለችው አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ፤ ሰው ለሆነ ዓላማ መትጋት እና መኖር እንደሚጠበቅበት ትመክራለች፡፡
በመከባበር እና መደናነቅ ሁሉም በየዘርፉ ቢሠራ ስኬት ላይ ይደረሳል፡፡ ድሮ በየዘርፉ የሚደነቁ በርካቶች የመኖራቸውን ያህል ዛሬም በቅንነት በመመልከት ለማድነቅ ልባችን ቢከፈት ብዙዎች አሉ ትላለች፡፡
በየመስኩ የምንፈልገው ስኬት ላይ ለመድረስ መትጋት ይጠበቅብናል፤ ያለትጋት ስኬት አይኖርምና በማለትም ጥረትን ያለተስፋ መቁረጥ ማስቀጠል እንደሚገባ መክራለች፡፡
በዮሐንስ ደርበው