Fana: At a Speed of Life!

የኮደርስ ስልጠና በዲጅታል ዘርፍ የኢትዮጵያን እድገት ለማሳለጥ ጉልህ ሚና አለው – አህመዲን መሃመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮደርስ ስልጠና በዲጅታል ዘርፍ የኢትዮጵያን የምጣኔ ሃብት እድገት ለማሳለጥ ፋይዳው የላቀ መሆኑን የአማራ ክልል የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አህመዲን መሃመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

በአማራ ክልል በዘጠኝ ወራት የተከናወኑ የኮደርስ ስልጠና አፈጻጸም በተመለከተ በደሴ ከተማ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

አህመዲን መሃመድ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ የኮደርስ ስልጠና በዲጅታል ዘርፍ የኢትዮጵያን የምጣኔ ሃብት እድገት ለማሳለጥና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ፋይዳው የላቀ ነው።

ለዚህም መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አንስተው፥ በተለይም ወጣቶች የኮደርስ ስልጠና እድል ተጠቃሚ ለመሆን መትጋት አለባቸው ብለዋል።

የኮደርስ ስልጠና በእውቀት እና ክህሎት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ በመሆኑ አጋጣሚው እንዳያመልጥ ሁሉም ሊሰለጥን እንደሚገባ አንስተዋል።

ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የስልጠና ክፍል በማዘጋጀትና ግብዓት በማሟላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ም/ሃላፊ አቶ የቻለ ይግዛው በበኩላቸው፥የኮደርስ ስልጠና በቴክኖሎጂ የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ ስልጠናውን በማጠናከር ቴክኖሎጂን፣ ክህሎትንና ዘመናዊ አሰራሮችን ለማስፋፋትና ለማሻሻል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ192 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ስልጠናውን እንዲወስዱ ታቅዶ እስካሁን ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ስልጠናውን ወስደዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.