Fana: At a Speed of Life!

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት ሥራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ም/ሃላፊ አቶ ደግነህ ቦጋለ እንዳሉት÷የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት ሥራ የቱሪስ ፍሰትን ለማሳደግና የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት ሚናው ጉልህ ነው፡፡

በክልሉ ፏፏቴዎች፣ ጥብቅ ደኖች፣ ትክል ድንጋዮች እና ዋሻዎችን ጨምሮ በርካታ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ የቱሪስት መስህቦች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ም/ሃላፊው÷ በዚህም 11 የቱሪስት መዳረሻዎችን በመለየት የማልማት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት 9 ወራት 447 ሺህ በላይ ቱሪስቶች በክልሉ የሚገኙ መስህቦችን የጎበኙ ሲሆን÷ ከዚህም 824 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡

ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግም ቢሮው አገልግሎት ሰጪ ተቋማትንና የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

አሁን ላይ በጢያ ትክል ድንጋይ ዙሪያ የሎጂዎች እና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተካልኝ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.