የኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ክህሎትን በማሳደግ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እንደሚያደርግ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የ5 ሚሊየን ኢትዮጵውያን ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ክህሎትን በማሳደግ በዘርፉ ተጨማሪ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የሚያደርግ መሆኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።
ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት ከመሰረተ ልማትና አስቻይ ስርዓት መዘርጋት በተጨማሪ የዲጂታል ክህሎት ያለው ማህበረሰብ አስፈላጊ ስለመሆኑም አስገንዝበዋል።
ስልጠናውን የተከታተሉ የመንግስት ሰራተኞች ለስራቸው ውጤታማነት እገዛ እያደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው÷ አዳዲስ የስራ እድል መፍጠር የቻሉ እንዳሉም ተናግረዋል።
የዲጂታል ክህሎትን በማሳደግ በዘርፉ ተጨማሪ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲመጣ ያደርጋልም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመርሐ ግብሩ የሚሰጠው ስልጠና ከዲጂታል ክህሎት በተጨማሪ እውቀትን መሰረት ያደረገና ምክንያታዊ ውሳኔዎችን መስጠት የሚያስችሉ ክህሎቶችን ማግኘት የሚቻልበት እንደሆነም ተናግረዋል።
የአምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና ሐምሌ 2016 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገ ሲሆን÷ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት ለመጨበጥ ያስችላል።