በኢትዮጵያ ታምርት መርሐ ግብር የኢትዮጵያን እድገት የሚያረጋግጡ ትላልቅ ተግባራት እየተከናወኑበት ነው – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ታምርት መርሐ ግብር የኢትዮጵያን እድገት የሚያረጋግጡ ትላልቅ ተግባራት እየተከናወኑበት መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ የሚገኘውን የኢትየጵያ ታምርት ኤክስፖን በመጎብኘት የግብርና ግብዓት የሚያቀነባብሩ፣ የማዕድን ምርት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች የሰውን እንቅስቃሴ የሚያቀላጥፉ ማሽኖች እና ሌሎች ተግባራትን ተመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በርካታ አስደናቂ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን እንደተመለከቱም ገልጸዋል።
በተለይ የኢትዮጵያን እድገት የሚያረጋግጡ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ግዙፍ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል፡፡
በኢትየጵያ ታምርት መርሐ ግብር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በኤክስፖ መቅረቡ ዜጎችን በማነቃቃትና አምራቾችን በማበረታታት በኩል ትልቅ ሚና የሚጫወቱ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሀገርን እድገት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አረጋ÷ የኢትየጵያ ታምርት ኤክስፖ ትልቅ ትርጉም ያለው እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሦስተኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ትናንት መክፈታቸው ይታወሳል፡፡