የማር ምርትን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውጤት አምጥቷል – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የማር ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ተናገሩ።
በጅማ ከተማ የማር ምርትን የሚያስተዋውቅ ንግድና ኤግዚቢሽን እየተካሄ ይገኛል።
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ላለፉት አራት አመታት በተሠራው የንብ ማነብ ስራ ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ2 ሚሊየን በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ጠቅሰው፤ ከማር ምርት አንጻር 220 ሺህ ቶን ምርት መገኘቱን ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ በክልሉ የዘመናዊ ቀፎ ክላስተሮችን በማሳደግ ከፍተኛ የማር ምርት ተገኝቷል ብለዋል።
ባለፉት አመታት በተሰራው ሥራ በክልሉ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ቁጥር ከሶስት ሚሊየን በላይ መድረሱን ጠቁመዋል።
የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር፤ ዞኑ ለንብ ማነብ ሥራ ከፍተኛ አቅም ያለው በመሆኑ በትኩረት እየተሰራበት እንደሆነ ገልጸው፤ በአንድ ቀፎ የሚመረተውን የማር መጠን ለማሳደግ በተሰራው ሥራ በቀፎ እስከ 36 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።
በአቤንኤዘር ታየ