በኮሪደር ልማት የመዲናዋን ቅርሶች በማደስ እንደ አዲስ ማስተዋወቅ ተችሏል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች የመዲናዋን ቅርሶች በማደስና ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ እንደ አዲስ እንዲተዋወቁ ማስቻላቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በመዲናዋ በበርካታ ቦታዎች የሚገኙ ቀደም ሲል ቅርስነታቸው ያልተለዩና የማይታወቁ ቅርሶች ጭምር ተለይተውና ታድሰው ለቱሪስት መስህብ ክፍት መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በፒያሳ፣ በአራት ኪሎ፣ በቸርችል ጎዳናና ማዘጋጃ ቤት አካባቢ የሚገኙ ቅርሶች መጠገናቸውና ለጎብኚዎች ክፍት መደረጋቸውንም ከንቲባዋ ለአብነት አንስተዋል።
የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ቅርሶቹንና ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጎብኘት እየመጡ ናቸው ብለዋል።
የተደበቁ ቅርሶች ተጠግነው፣ ጥበቃ እንዲደረግላቸውና የአስተዳደር ስራው እንዲጠናከር መደረጉን አመላክተዋል።
የኮሪደር ልማት የከተማዋን ዋና ዋና ችግሮች በመቀነስ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ አረንጓዴ ሽፋን መጨመር፣ የትራፊክ ፍሰት ማሻሻል፣ የመኪና ማቆሚያ እጥረት መቀነስ እና የትራፊክ አደጋን ከመከላከል አንጻር የተገኙ ለውጦችን ጠቁመዋል።
በኮሪደር ልማቱ የመሰረተ ልማት ተቋማት በቅንጅት ሰርተው ውጤታማ መሆን፣ በፍጥነት ጀምሮ መጨረስ እንዲሁም ከሳምንት እስከ ሳምንት ለ24 ሰዓት መስራት እንደሚቻል ያመላከተ ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ ቆርጠን ከሰራን ምንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ ነው ያሉት ከንቲባዋ÷ ልማቱ እንዲሳካ የባህል ለውጥ ማምጣት ይጠይቃል፤ ጊዜ ይፈጃል የሚለውን አመለካከት የቀየረ እንደሆነ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የከተማዋ ወንዞች ተፈጥሯዊ ማንነታቸውን አጥተው ከጸጋነታቸው ወደ አደጋ ማድረስ ተቀይረው እንደነበር አንስተው÷ የወንዞቹ ምንጮች መድረቃቸውን፣ የተፈጥሮ ውሃቸውን ማጣታቸውንና የመጸዳጃና የጎርፍ ፍሳሽ ማጠራቀሚያ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በወንዞች ዙሪያ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች በብክለትና በጎርፍ አደጋ ሳቢያ ጤናቸው ተቃውሷል፤ ህይወታቸው ተቀጥፏል ብለዋል።
እነዚህን ችግሮች በማየት ወንዞችን ከአደጋ አድራሽነት ወደ ቱሪስት መዳረሻነት እንዲቀየሩ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በመልማት ላይ የሚገኙ ወንዞች ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተከናውነዋልም ነው ያሉት።
የወንዞች ዳርቻዎች ለቱሪስት መዳረሻ፣ የገቢ ማግኛ እንዲሁም የመዝናኛ ቦታዎች እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።