ወጣቱ ትውልድ የዘመኑ አርበኛ ሊሆን ይገባል – የፈጠራ ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ወጣቱ ትውልድ የዘመኑ አርበኛ ሊሆን ይገባል ሲሉ በሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር ላይ የተሳተፉ የፈጠራ ባለሙያዎች ገለጹ።
የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት 4ኛው የሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር በመካሄድ ላይ ይገኛል።
እስከ መጪው ቅዳሜ በሚቀጥለው ውድድር ላይ በርካታ የፈጠራ ባለሙያዎች የፈጠራ ውጤቶቻቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከውድድሩ ተሳታፊዎች መካከል ከቱርክ ሃገር ይመጣ የነበረውን የእህል መውቂያ ማሽን በመቅዳት መስራት የቻለው ወርቅአፈራሁ ሻፊ አንዱ ነው።
ወርቃፈራሁ ይህንን የስንዴ መውቂያ ማሽን በሀገር ውስጥ መስራት ከመቻሉም ባሻገር ከስንዴ በተጨማሪ በኢትዮጵያ በስፋት የሚመረተውን ጤፍ መውቃት የሚያስችል መሆኑን ተናግሯል።
የድሮ አባቶቻችን አስገራሚ የጀግንነት ታሪኮችን ሰርተው አልፈዋል፤ እኛ በዚህ ዘመን የምንገኝ ወጣቶች ደግሞ ጠላታችን ድህነት በመሆኑ እንደ አባቶቻችን የምግብ ችግራችንን ለመፍታት እየሰራን ነው ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኘውን የሽመና ስራ በማዘመንና ቀላል ማድረግ የሚያስችል የጨርቅ መስሪያ ማሽን መስራታቸውን የገለጸው ደግሞ ደምስ ኪዳኔ የተባለው ሌላኛው የውድድሩ ተሳታፊ ነው።
የፈጠራ ባለሙያው እንደሚለው የጨርቅ መስሪያ ማሽኑ ከሞተሩ በቀር ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ቁሳቁሶች የተሰራ ነው።
ማሽኑ የጅንስና የጣቃ ጨርቆችን ጨምሮ የተለያዩ አይነት የጨርቅ ምርቶችን ማምረት የሚያስችል እንደሆነ ገልጾ፥ የሀገራችን ምርት የሆኑ ልብስ መልበስና ማጌጥ በዚህ ዘመን ማድረግ ከምንችላቸው አርበኝነቶች አንዱ እንደሆነ አስረድቷል።
ሌላኛው የውድድሩ ተሳታፊ መሐመድ ተስፋዬ በበኩሉ፤ በኢትዮጵያ መሰራት ያለባቸው ብዙ ዘርፎች መኖራቸውን በመግለጽ፥ አባቶቻችን ጠላትን ድል እንዳደረጉ ሁሉ እኛም ድህነትን ድል የምናደርግበትን ስራ መስራት ይጠበቅብናል ሲል ተናግሯል፡፡
በተለይም በትምህርት፣ በምርምርና በፈጠራ ላይ ትኩረት አድርገን ብንሰራ የውጪ ሀገራትን እጅ ሳናይ በራሳችን ስራ መኩራት እንችላለን በማለትም አክሏል።
በዮናስ ጌትነት