ኢትዮጵያ የፓኪስታንና አፍሪካ ሀገራት የንግድ ትስስር ለማጠናከር ያለመ ጉባዔ እንደምታስተናግድ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በፓኪስታንና አፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ አጋርነትና የንግድ ትስስር ለማጠናከር ያለመ ጉባዔ እንደምታስተናግድ ተገልጿል።
5ኛው የፓኪስታን – አፍሪካ ንግድ ጉባዔ ከመጪው ግንቦት 7 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሻሪፍ ሚያን ፓኪስታን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የንግድ ትበብር ለማጠናከር እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭና ተደራሽ በመሆኗ ጉባዔውን ለማስተናገድ እንደተመረጠችም አመላክተዋል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የንግድ ጉባዔው ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማስተዋወቅ ያስችላል ብለዋል።
ጉባዔውን ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ መመረጧ የሀገራቱ ግንኙነት ይበልጥ መጠናከሩን እንደሚያሳይ አስገንዝበዋል።
በጉባዔው ከ100 በላይ ትላልቅ የፓኪስታን ንግድ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።
ከናይጀሪያ፣ ዩጋንዳ፣ ጋና፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና ቡሩንዲ የተወጣጡ ኩባንያዎች በጉባዔው እንደሚሳተፉም ተመላክቷል።
ባለሃብቶች በፓኪስታን – አፍሪካ ንግድ ጉባዔ ላይ በመሳተፍ ከተለያዩ ሀገራት ኩባንያዎች ጋር የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩ ጥሪ ቀርቧል።
ጉባዔውን የፓኪስታን ንግድ ልማት ባለስልጣን፣ በኢትዮጵያ የፓኪስታን ኤምባሲ የንግድ ዘርፍ እና የፓኪስታን – አፍሪካ ንግድ ልማት ጉባዔ በጋራ ማዘጋጀታቸው ተገልጿል።