በኢትዮጵያ ላይ የሚመዘዙ አጀንዳዎችን በብቃት መመከት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል – ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እና ብሔራዊ ጥቅሞቿ ላይ የሚመዘዙ አጀንዳዎችን በብቃት መመከት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች “የመሀል ዘመን” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ሀገራዊ ሰነድ ላይ በተወያዩበት ወቅት ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር)፤ ተቋማትና ግለሰቦች ኃላፊነታቸውን መወጣት ከቻሉ የኢትዮጵያ የብልጽግና ሕልሞች የሚሳኩ መሆናቸውን ያለፉት ዓመታት ስኬቶች ምስክሮች ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ማስገንዘብ፣ የመንግሥትን ፖሊሲዎች፣ መነሣሣቶች፣ ዕቅዶች፣ አፈጻጸሞች እና ውጤቶች ማሳወቅ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ኃላፊነት እንደሆነ አስታውሰው፤ ዘርፉን በአጀንዳ መምራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እና ብሔራዊ ጥቅሞቿ ላይ የሚመዘዙ አጀንዳዎችን በብቃት መመከት በዘርፉ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመልክተዋል።
ለመድረኩ የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች እድገት እያስመዘገበች መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህንን ለውጥ በማስቀጠል የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ለማድረስ በውስጥና በውጭ ያሉ ክፍተቶችንና ተጋላጭነቶችን ነቅሶ በማውጣት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሀገራችን በለውጥ ሂደት በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ፈተናዎችን ተሻግራለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ድርቅ፣ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽ፣ የእርስ በርስ ግጭትና መፈናቀል ለውጡን የፈተኑ ጉዳዮች ነበሩ ብለዋል።
የሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት እና የአመራሩ ቁርጠኝነት እና ብስለት የተሞላበት አመራር ለውጡን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገራቸውንም ተናግረዋል።
የሕዝብን ጥያቄዎች በመመለስ፣ አካታች የፖለቲካ ሥርዓት በመዘርጋት፣ የኢኮኖሚ ሪፎርም በማድረግና ዕድገቱን በማስቀጠል፣ የትርክት ለውጥ በማድረግና ፈተናዎችን በመቋቋም በርካታ ስኬቶች በየዘርፉ መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።
እነዚህ ስኬቶች የፈጠሩት መለስተኛ እርካታ ወደማይቀለበሰው የብልጽግና መዳረሻ የሚደረገውን ጉዞ እንዳያሰናክሉ በብስለት ማለፍ እንደሚገባ መግለጻቸውን የአገልግሎቱ መረጃ አመላክቷል።
በስኬቶች ሊደበቁ የሚችሉ ውስጣዊ ክፍተቶችን ያለማቅማማት መፍታት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።